ሐጌ 2:16-22 NASV

16 አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደ ሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ አምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ፤

17 የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል እግዚአብሔር፤

18 ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤

19 በጐተራ የቀረ ዘር አሁንም ይገኛልን? የወይኑና የበለሱ ዛፍ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ እስካሁን አላፈሩም።“ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’ ”

20 በወሩ ሃያ አራተኛ ቀን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፤

21 “ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል ሰማያትንና ምድርን እንደማናውጥ ንገረው፤

22 የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል አጠፋለሁ፤ ሠረገሎችንና ሠረገለኞችን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውም በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።