ሩት 2:13-19 NASV

13 እርሷም መልሳ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ምንም እንኳ፣ ከሴት ሠራተኞችህ እንደ አንዲቱ መቈጠር የማይገባኝ ብሆንም፣ እንድጽናና አድርገኸኛል፤ እንዲሁም እኔን አገልጋይህን በመልካም ንግግር ደስ አሰኝተኸኛል፤ ስለዚህ ሞገስህ እንዳይለየኝ እለምንሃለሁ” አለችው።

14 በምሳ ሰዓት ቦዔዝ፣ “ወደዚህ ቀረብ በዪ፤ እንጀራም ወስደሽ በወይን ሆምጣጤው አጥቅሽ” አላት።እርሷም ከአጫጆች አጠገብ እንደ ተቀመጠች፣ ቦዔዝ የተጠበሰ እሸት ሰጣት፤ የቻለችውንም ያህል በልታ ጥቂት ተረፋት።

15 ለመቃረም ስትነሣም፣ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “በነዶው መካከል እንኳ ብትቃርም ክፉ አትናገሯት፤

16 ይልቁንም ከየታሰረው ነዶ ላይ ጥቂት ጥቂቱን ዘለላ እየመዘዛችሁ በመጣል እንድታነሣው ተዉላት፤ አታስቀይሟት።”

17 ስለዚህ ሩት እስኪመሽ ድረስ ከአዝመራው ላይ ቃረመች፤ ከዚያም የሰበሰበችውን ገብስ ወቃች፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያም ያህል ሆነ።

18 ያንንም ይዛ ወደ ከተማ ሄደች፤ አማቷም የሰበሰበችው ምን ያህል እንደሆነም አየች፤ እንዲሁም ሩት የሚበቃትን ያህል ከበላች በኋላ አስተርፋ የነበረውን አውጥታ ለእርሷ ሰጠቻት።

19 አማቷም፣ “ዛሬ የቃረምሽው ከየት ነው? የትስ ቦታ ስትሠሪ ዋልሽ? መልካም ነገር ያደረገልሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት። ከዚያም ሩት ስትሠራ ስለዋለችበት ስፍራ ባለቤት ለአማቷ ነገረቻት፤ እርሷም፣ “ዛሬ ስቃርም የዋልሁበት አዝመራ ባለቤት፣ ስሙ ቦዔዝ ይባላል” አለቻት።