ሩት 4:1-5 NASV

1 ቦዔዝም ወደ ከተማዪቱ በር አደባባይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ እርሱም የመቤዠት ቅድሚያ ያለው የቅርብ ዘመድ በመጣ ጊዜ፣ “ወዳጄ ሆይ፤ ወደዚህ ና፣ አጠገቤም ተቀመጥ” አለው፤ ስለዚህም ሰውየው ሄዶ ተቀመጠ።

2 ቦዔዝ ከከተማዪቱ ሽማግሌዎች ዐሥሩን ጠርቶ፣ “እዚህ ተቀመጡ” አላቸው፤ እነርሱም ተቀመጡ።

3 ከዚያም የመቤዠት ቅድሚያ ያለውን ቅርብ የሥጋ ዘመድ እንዲህ አለው፤ “ከሞዓብ የተመለሰችው ኑኃሚን፣ የወንድማችንን የአቤሜሌክን ጢንጦ መሬት ልትሸጥ ነው።

4 አንተም ይህንኑ ጒዳይ ማወቅ አለብህ ብዬ ስላሰብሁ፣ አሁን እዚህ በተቀመጡትና በሕዝቤም ሽማግሌዎች ፊት እንድትገዛው ላሳስብህ ወደድሁ፤ አሁንም ራስህ የምትቤዠው ከሆነ ልትቤዠው ትችላለህ፤ ለዚህ ከአንተ ቅድሚያ የሚኖረው የለም፤ ይህን የማታደርግ ከሆነ ግን ከአንተ ቀጥሎ የሚገባኝ ስለ ሆንሁ፣ ንገረኝና ልወቀው።” ሰውየውም “እኔ እቤዠዋለሁ” አለ።

5 ከዚያም ቦዔዝ፣ “እንግዲህ መሬቱን ከኑኃሚንና ከሞዓባዊቷ ከሩት ላይ በምትገዛበት ዕለት የሟቹን ስም በርስቱ ለማስጠራት ሚስቱንም አብረህ መውሰድ አለብህ” አለው።