ነህምያ 13:5-11 NASV

5 ከዚህ በፊት የእህል ቍርባኑ፣ ዕጣኑ፣ የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች፣ የእህሉ ዐሥራትና፣ ለሌዋውያን፣ ለመዘምራንና ለበር ጠባቂዎች የታዘዘው አዲሱ ወይንና ዘይት፣ ለካህናቱም የሚመጣው ስጦታ ይቀመጥበት የነበረውን ትልቁን የዕቃ ቤት እንዲኖርበት ሰጥቶት ነበር።

6 ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም፤ ምክንያቱም በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ ሠላሳ ሁለተኛ ዓመት ተመልሼ ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበር። ከጥቂት ጊዜም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ጠይቄ

7 ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስሁ፤ በዚያም ኤልያሴብ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ አንድ መኖሪያ ክፍል በመስጠት የፈጸመውን ክፉ ድርጊት ተረዳሁ።

8 እኔም በጣም ዐዘንሁ፤ የጦብያንም የቤት ዕቃ ሁሉ ከክፍሉ እያወጣሁ ወደ ውጭ ጣልሁ።

9 ክፍሎቹንም እንዲያነጹ ትእዛዝ ሰጠሁ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች፣ የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን ጭምር መልሼ አስገባሁ።

10 እንዲሁም ለሌዋውያን የተመደበው ድርሻ እንዳልተሰጣቸውና አገልግሎቱን በኀላፊነት የሚመሩ ሌዋውያንና መዘምራን ሁሉ ወደየርስታቸው መመለሳቸውን ተረዳሁ።

11 ስለዚህ ሹማምቱን ገሥጬ፣ “ቤተ መቅደሱ እስከዚህ ቸል የተባለው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው። ከዚያም እነርሱን በአንድነት ሰብስቤ ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ አደረግሁ።