1 ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ማማ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ማማ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤
2 ቀጥሎ ያለውንም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ እነርሱ ከሠሩት ቀጥሎ ደግሞ የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።
3 የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።
4 የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤