ነህምያ 3:12-18 NASV

12 የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የአሎኤስ ልጅ ሰሎም ከሴት ልጆቹ ጋር በመሆን ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ።

13 “የሸለቆ በር” ተብሎ የሚጠራውን የሐኖንና የዛኖ ነዋሪዎች ዐደሱት፤ መልሰው ሠሩት፤ ከሠሩትም በኋላ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጁ። እንዲሁም “የቆሻሻ መጣያ በር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን አንድ ሺህ ክንድ ቅጥር መልሰው ሠሩ።

14 “የቈሻሻ መጣያ በር” ተብሎ የሚጠራው የቤት ሐካሪም አውራጃ ገዥ የሆነው የሬካብ ልጅ መልክያ መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራ በኋላም መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖረ።

15 የምጽጳ አውራጃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም “የምንጭ በር” ተብሎ የሚጠራውን መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራም በኋላ ከድኖ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖረ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጀ። “የንጉሥ አትክልት ቦታ” ተብሎ በሚጠራው አጠገብ የሚገኘውን የሼላን መዋኛ ግንብም፣ ከዳዊት ከተማ ጀምሮ ቍልቍል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ መልሶ ሠራ።

16 ከእርሱም በኋላ የቤት ጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር ትይዩ እስከ ሰው ሠራሹ ኵሬና “የጀግኖች ቤት” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን መልሶ ሠራ።

17 ከእርሱ ቀጥሎ ሌዋውያኑ በባኒ ልጅ በሬሁ ሥር ሆነው የዕድሳት ሥራ ሠሩ። ከእርሱ ቀጥሎ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ ሐሸብያ አውራጃውን መልሶ ሠራ።

18 ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ደግሞ የሌላው የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይና በእርሱም ሥር የነበሩት የአገሩ ሰዎች መልሰው ሠሩ።