ነህምያ 9:18-24 NASV

18 የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብፅ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።

19 “ከርኅራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ ቀን የደመናው ዐምድ በመንገዳቸው ላይ መምራቱን፣ ሌሊትም የእሳቱ ዐምድ በሚሄዱበት ላይ ማብራቱን አላቆመም።

20 ያስተምራቸው ዘንድ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናውን ከአፋቸው አልከለከልህም፤ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው።

21 በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።

22 “በሩቅ የሚገኙትን ድንበሮች እንኳ ሳይቀር፣ መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፣ የባሳን ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ።

23 ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛሃቸው፤ አባቶቻቸው ገብተው እንዲወርሱ ወዳዘዝሃቸውም ምድር አገባሃቸው።

24 በምድሪቱ ወንዶች ልጆቻቸው ገቡባት፤ ወረሷትም። በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን በፊታቸው አንበረከክህ፤ ያሻቸውን ያደርጉባቸው ዘንድ ከነዓናውያንን ከንጉሦቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው።