ነህምያ 9:20-26 NASV

20 ያስተምራቸው ዘንድ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናውን ከአፋቸው አልከለከልህም፤ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው።

21 በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።

22 “በሩቅ የሚገኙትን ድንበሮች እንኳ ሳይቀር፣ መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፣ የባሳን ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ።

23 ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛሃቸው፤ አባቶቻቸው ገብተው እንዲወርሱ ወዳዘዝሃቸውም ምድር አገባሃቸው።

24 በምድሪቱ ወንዶች ልጆቻቸው ገቡባት፤ ወረሷትም። በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን በፊታቸው አንበረከክህ፤ ያሻቸውን ያደርጉባቸው ዘንድ ከነዓናውያንን ከንጉሦቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው።

25 የተመሸጉ ከተሞቻቸውንና የሰባውን ምድር ያዙ፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሞሉ ቤቶቻቸውን፣ የተቈፈሩ የውሃ ጒድጓዶቻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የፍሬ ዛፎች ያዙ። እስኪጠግቡ በሉ፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ ተሰኙ።

26 “ነገር ግን እንቢተኞች ሆኑ፤ ዐመፁብህም፤ ሕግህንም አሽቀንጥረው ጣሉ፤ ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩት ነቢያትህን ገደሉ፤ አስጸያፊ የስድብ ቃልም ተናገሩ።