ነህምያ 9:32-38 NASV

32 “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ ቃል ኪዳንህንና ዘላለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራህ አምላክ ሆይ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችንና በመሪዎቻችን፣ በካህናታችንና በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ መከራ በፊትህ እንደ ቀላል ነገር አይታይ።

33 በደረሰብን ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛ በደለኞች ነን፤ አንተ ግን ትክክለኛውን አደረግህ።

34 ነገሥታታችን፣ መሪዎቻችን፣ ካህናታችንና አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዞችህን ወይም የሰጠሃቸውን ማስጠንቀቂያዎች አልሰሙም።

35 በገዛ መንግሥታቸው፣ በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህና በፊታቸውም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም ምድር እንኳ፣ አንተን አላገለገሉም፤ ከክፉ መንገዳቸውም አልተመለሱም።

36 “እነሆ፤ ዛሬም ባሮች ነን፤ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ባሮች ነን።

37 ከኀጢአታችን የተነሣ የተትረፈረፈው መኸር ሲሳይ የሆነው በላያችን ላስቀመጥሃቸው ነገሥታት ነው፤ እነርሱም ደስ እንዳሰኛቸው በሰውነታችንና በቀንድ ከብቶቻችን ላይ ያዛሉ። እኛም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንገኛለን።

38 “ከዚህ ሁሉ የተነሣም ጽሑፍ ላይ በማስፈር ግዴታ የምንገባበትን የውል ስምምነት እናደርጋለን፤ መሪዎቻችን፣ ሌዋውያኖቻችንና ካህናቶቻችንም ማኅተሞቻቸውን ያኖሩበታል።”