ኢዩኤል 3:2-8 NASV

2 አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤ምድሬን ከፋፍለዋል፤ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና።

3 በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ወንዶች ልጆችን በዝሙት አዳሪዎች ለወጡ፤ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣ሴቶች ልጆችን ሸጡ።

4 “ጢሮስና ሲዶና እንዲሁም እናንተ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሁሉ ሆይ፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ምን አላችሁ? ስላደረግሁት ነገር ብድር ልትመልሱልኝ ነውን? የምትመልሱልኝ ከሆነ፣ በፍጥነትና በችኰላ እናንተ ያደረጋችሁትን በራሳችሁ ላይ መልሼ አደርግባችኋለሁ።

5 ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤ የተመረጠውንም ንብረቴን ተሸክማችሁ ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አስገብታችኋልና።

6 ከገዛ ምድራቸው ልታርቋቸው፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለግሪኮች ሸጣችኋቸው።

7 “እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ።

8 ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሰዎች ሸጣለሁ፤ እነርሱም መልሰው በሩቅ ላሉት ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።