2 ቆሮንቶስ 1:18-24 NASV

18 እግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ ሁሉ፣ ለእናንተ የምንናገረው ቃላችን፣ “አዎን” እና “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤

19 ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ “አዎን” ነው።

20 በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።

21 እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤

22 የእርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።

23 ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ እግዚአብሔር ይመስክርብኝ።

24 ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለ ሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም።