1 መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።
2 እስከዚያው ግን የሰማዩን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን እንቃትታለን፤
3 በርግጥ ከለበስነው ራቊታችንን ሆነን አንገኝም።
4 በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም።
5 ለዚህ ዐላማ ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ሊመጣ ላለው ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን መያዣ አድርጎ የሰጠንም እርሱ ነው።