9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።
10 ስለዚህ ጒዳይ የምሰጣችሁ ጠቃሚ ምክር ይህ ነው፤ ባለፈው ዓመት በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤
11 አሁንም የጀመራችሁትን ተግባር በዐቅማችሁ መጠን ከፍጻሜ አድርሱት፤ ይህም ለመስጠት የነበራችሁ በጎ ፈቃድ እውን እንዲሆን ነው።
12 ለመስጠት በጎ ፈቃድ ካለን ስጦታው ተቀባይነት የሚያገኘው ባለን መጠን ስንሰጥ እንጂ፣ በሌለን መጠን ለመስጠት ስንሞክር አይደለም።
13 ይህንን የምንለው እናንተ ተቸግራችሁ ሌሎች ይድላቸው ለማለት ሳይሆን፣ ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው።
14 በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጒድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጒድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ።
15 ይህም፣ “ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂት የሰበሰበም አልጐደለበትም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።