2 ቆሮንቶስ 9:1-7 NASV

1 ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም።

2 ምክንያቱም ሌሎችን ለመርዳት ያላችሁን በጎ ፈቃድ ዐውቃለሁ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እናንተ በአካይያ የምትኖሩ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆናችሁ ለመቄዶንያ ሰዎች አፌን ሞልቼ ተናግሬአለሁ፤ ቅን ፍላጎታችሁም ብዙዎችን ለበጎ ሥራ አነሣሥቶአል።

3 እንግዲህ በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደ ተናገርሁት ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ ወንድሞችን ልኬአለሁ።

4 ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር መጥተው ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም ያን ያህል በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን።

5 ስለዚህ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡና ከዚህ በፊት ለመስጠት ቃል የገባችሁትን ስጦታ አጠናቃችሁ እንድትጠብቋቸው፣ እነርሱን መለመን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ በልግስና ለመስጠት ያሰባችሁት ነገር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተዘጋጀ ይሆናል።

6 ይህን አስታውሱ፤ ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል።

7 እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል።