10 በቤቴ መብል እንዲኖር፣ እኔንም በዚህ እንድትፈትኑኝ ዐሥራቱን ሁሉ ወደ ጐተራ አስገቡ፤” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።
11 ስለ እናንተ ተባዩን እገሥጻለሁ፤ አዝመራችሁን አይበላም፤ ዕርሻ ላይ ያለ የወይን ተክላችሁም ፍሬ አልባ አይሆንም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።
12 “ከዚያም በኋላ የተድላ ምድር ስለምትሆኑ ሕዝቦች ሁሉ የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።
13 “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ተናግራችኋል” ይላል እግዚአብሔር።“እናንተ ግን፣ ‘በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድን ነው?’ ትላላችሁ።
14 “እንዲህም ብላችኋል፤ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ በማድረግና በእግዚአብሔር ጸባኦት ፊት ሐዘንተኞች ሆነን በመመላለስ ምን ተጠቀምን?
15 አሁን ግን ትዕቢተኞችን ቡሩካን እንላቸዋለን፤ ክፉ አድራጊዎች ይበለጽጋሉ፤ እግዚአብሔርን የሚፈታተኑትም ያመልጣሉ።’ ”
16 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔር አዳመጠ፤ ሰማቸውም፤ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ስሙን ለሚያከብሩ በእርሱ ፊት የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።