5 በእርግጥ የወይን ጠጅ አታሎታል፤ትዕቢተኛ ነው፤ ከቶ አያርፍም፤እንደ ሲኦል ስስታም ነው፣እንደ ሞት ከቶ አይጠግብም፤ሕዝቦችን ለራሱ ይሰበስባል፤ሰዎችንም ሁሉ ማርኮ ይወስዳል።
6 “ታዲያ በእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ላይ በማፌዝና በመዘበት እንዲህ እያሉ ሁሉም አይሣለቁበትምን?“የተሰረቀውን ሸቀጥ ለራሱ ለሚያከማች፣ራሱን በዐመፅ ባለጠጋ ለሚያደርግ ወዮለት!ይህ የሚቀጥለውስ እስከ መቼ ነው?”
7 ባለ ዕዳ ያደረግሃቸው ድንገት አይነሡብህምን?ነቅተውስ አያስደነግጡህምን?በእጃቸውም ትወድቃለህ።
8 አንተ ብዙ ሕዝብ ስለ ዘረፍህ፣የተረፉት ሕዝቦች ይዘርፉሃል፤የሰው ደም አፍሰሃልና፤አገሮችንና ከተሞችን፣ በውስጣቸው የሚኖሩትን ሁሉ አጥፍተሃል።
9 “በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን ለሚገነባ፣ከጠላት እጅ ለማምለጥ፣ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት!
10 የብዙ ሰዎች ነፍስ እንዲጠፋ አሢረሃል፤በገዛ ቤትህ ላይ ውርደትን፣ በራስህም ላይ ጥፋትን አምጥተሃል።
11 ድንጋይ ከቅጥሩ ውስጥ ይጮኻል፤ከዕንጨት የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይመልሱለታል።