24 ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደበቀ፤ የወር መባቻ በዓል በተከበረበት ጊዜ፣ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ፤
25 ንጉሡ እንደ ወትሮው በግድግዳው አጠገብ ተቀመጠ፤ ዮናታን ከፊት ለፊቱ፣ አበኔር ደግሞ ከአጠገቡ ተቀመጡ፤ የዳዊት መቀመጫ ግን ባዶ ነበር።
26 ሳኦልም፣ “ዳዊት በሥርዐቱ መሠረት እንዳ ይነጻ የሚያደርገው አንድ ነገር ገጥሞታል፤ በእርግጥም አልነጻም” ብሎ ስላሰበ፣ በዚያ ቀን ምንም አልተናገረም።
27 በማግስቱም፣ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን የዳዊት መቀመጫ ባዶ ነበር፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን፣ “የእሴይ ልጅ ትናንትናም፣ ዛሬም ግብር ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
28 ዮናታንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ አጥብቆ ለመነኝ።
29 እርሱም ‘ቤተ ሰባችን በከተማዪቱ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያደርግ በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛልና ልሂድ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ’ አለኝ። በንጉሡ ግብር ላይ ሳይገኝ የቀረውም በዚህ ምክንያት ነው።”
30 ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አንተ የዚያች ጠማማና ዐመፀኛ ሴት ልጅ! ለአንተው ለራስህ ውርደት፣ ለወላጅ እናትህም ዕፍረት ከሚሆነው ከእሴይ ልጅ ጋር መግጠምህን የማላውቅ መሰለህ?