5 ይሁን እንጂ ነቢዩ ጋድ ዳዊትን፣ “በዐምባው ውስጥ አትቈይ፤ ሂድና ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ተነሥቶ ወደ ሔሬት ጫካ ገባ።
6 ሳኦልም፣ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን በሰማ ጊዜ፣ በጊብዓ ኰረብታ ላይ በአጣጥ ዛፍ ሥር፣ ጦሩን በእጁ ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ ሹማምቱም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር።
7 ሳኦልም እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የብንያም ሰዎች ስሙ! በውኑ የእሴይ ልጅ ዕርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን?
8 በእኔ ላይ የዶለታችሁት ለዚህ ነውን? ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ሲያደርግ ማንም አልነገረኝም፤ ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ልጄ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሣሣቱን ከእናንተ ስለ እኔ ተቈርቍሮ የነገረኝ ማንም የለም።”
9 ነገር ግን እዚያ ከነበሩት የሳኦል ሹማምት ጋር ቆሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ እንዲህ አለ፣ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወዳለው ወደ አኬጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ።
10 አቢሜሌክም እግዚአብሔርን ጠየቀለት፤ እንዲሁም ስንቅና የፍልስጥኤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው።”
11 ከዚያም ንጉሡ፣ የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን፣ በኖብ ካህናት የነበሩትን የአባቱን ቤተ ሰብ በሙሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ።