10 ደቀ መዛሙርቱም፣ “ታዲያ የኦሪት ሕግ መምህራን፣ ኤልያስ አስቀድሞ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
11 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ መጥቶ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፤
12 ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቶአል፤ ሆኖም የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። እንዲሁም የሰው ልጅ በእጃቸው መከራን ይቀበላል።”
13 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ተረዱ።
14 ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤
15 “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤
16 ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።”