ማቴዎስ 17 NASV

የኢየሱስ መልክ በቅጽበት መቀየር

1 ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ።

2 በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።

3 ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

4 ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ በዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው።

5 እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።

6 ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።

7 ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው።

8 ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም።

9 ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው።

10 ደቀ መዛሙርቱም፣ “ታዲያ የኦሪት ሕግ መምህራን፣ ኤልያስ አስቀድሞ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።

11 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ መጥቶ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፤

12 ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቶአል፤ ሆኖም የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። እንዲሁም የሰው ልጅ በእጃቸው መከራን ይቀበላል።”

13 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ተረዱ።

ኢየሱስ የሚጥል በሽታ ያለበትን ልጅ ፈወሰ

14 ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤

15 “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤

16 ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።”

17 ኢየሱስም፣ “አንት የማታምን ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤ እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ። ልጁን ወደዚህ አምጡት” አለ።

18 ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸውና ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነ።

19 ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።

20 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህንን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤

21 የዚህ ዓይነቱ ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በስተቀር አይወጣም።”

22 በገሊላ ተሰባስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “የሰውን ልጅ አሳልፈው ለሰዎች ይሰጡታል፤

23 ይገድሉታልም፤ እርሱም በሦስተኛው ቀን ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱም እጅግ አዘኑ።

ስለ ቤተ መቅደስ ግብር ክፍያ

24 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱ ግብር ተቀባዮች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” አሉት።

25 እርሱም፣ “ይከፍላል እንጂ” አላቸው።ጴጥሮስ ወደ ቤት እንደ ገባ ኢየሱስ በቅድሚያ፣ “ስምዖን፤ የምድር ነገሥታት ግብር ወይም ቀረጥ የሚቀበሉት ከራሳቸው ልጆች ወይስ ከሌሎች ይመስልሃል?” አለው።

26 ጴጥሮስም፣ “ከሌሎች ነው የሚቀበሉት” አለው።ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እንግዲያውስ ልጆች ነጻ ናቸው፤

27 ሆኖም እንዳናስቀይማቸው ሄደህ መንጠቆህን ወደ ባሕር ጣል፤ መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት የምታገኘውን አንድ እስታቴር በእኔና በአንተ ስም ክፈል።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28