18 ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው።
19 በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።
20 ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት።
21 ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።
22 ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው።
23 ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ።
24 ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር።