3 ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ ሎሌዎችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር።
4 ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው።
5 እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር።
6 ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።
7 እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።
8 ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ፣ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤
9 ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።