1 “እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጒረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው፤
2 በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤
3 በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል።
4 የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል።
5 እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።”
6 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።
7 ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ።
8 ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም።
9 በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል።
10 ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።”
11 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤
12 ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የእርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሎአቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም።
13 የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው።
14 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤
15 ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ።
16 ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ።
17 መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወደኛል።
18 ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”
19 ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ።
20 ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙ ታለችሁ?” አሉ።
21 ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።
22 በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ጊዜውም ክረምት ነበረ፤
23 ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ግቢ፣ በሰሎሞን መመላለሻ ያልፍ ነበር፤
24 አይሁድም ከበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት።
25 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሳላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤
26 እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤
27 በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤
28 እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም።
29 እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም።
30 እኔና አብ አንድ ነን።”
31 አይሁድ ሊወግሩት እንደ ገና ድንጋይ አነሡ፤
32 ኢየሱስ ግን፣ “ከአብ የሆኑ ብዙ ታላላቅ ታምራትን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ ከእነዚህ ስለ የትኛው ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው።
33 አይሁድም፣ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለ የትኛውም አይደለም” ብለው መለሱለት።
34 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሕጋችሁ፣ ‘እናንት አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን?
35 የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጻሕፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ፣
36 ታዲያ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሃል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ?
37 አባቴ የሚያደርገውን ባላደርግ አትመኑኝ፤
38 የማደርገው ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ።”
39 እንደ ገናም ሊይዙት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አመለጠ።
40 ከዚያም ኢየሱስ፣ ቀደም ሲል ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደነበረበት፣ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተመለሰ፤ በዚያም ሰነበተ፤
41 ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “ዮሐንስ አንድም ታምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ።
42 በዚያም ስፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ።