23 ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር።
24 ስለዚህ፣ “ዕጣ ተጣጥለን ለሚደርሰው ይድረስ እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፣“ልብሴን ተከፋፈሉት፤በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።ወታደሮቹ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።
25 በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር።
26 በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤
27 ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት።
28 ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ።
29 በዚያም የሆመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤