39 እነርሱም፣ “አባታችንስ አብርሃም ነው” ብለው መለሱለት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ፣ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር።
40 ከእግዚአብሔር ሰምቼ እውነቱን የነገርኋችሁን እኔን ለመግደል ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል፤ አብርሃም ግን እንዲህ አላደረገም።
41 እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ የሚያደርገውን ነው።”እነርሱም፣ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አባታችንም አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲሉ መለሱለት።
42 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እርሱ ላከኝ እንጂ በገዛ ራሴ አልመጣሁም።
43 የምናገረውን ለምን አታስተውሉም? ምክንያቱም ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው።
44 እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው፤
45 እኔ ግን እውነት ስለምናገር አታምኑኝም።