17 ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢ አታችሁ አላችሁ ማለት ነው።
18 እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው።
19 ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።
20 ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል።
21 ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና።
22 ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤
23 ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት።