1 ቆሮንቶስ 4 NASV

የክርስቶስ ሐዋርያት

1 እንግዲህ ሰው ሁሉ እኛን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮችና እንደ እግዚአብሔር ምስጢር ባለ ዐደራዎች ሊቈጥረን ይገባል።

2 ባለ ዐደራዎችም ታማኝ ሆነው መገኘት አለባቸው።

3 በእናንተም ሆነ በሰዎች የፍርድ ሸንጎ ቢፈረድብኝ እኔ በበኩሌ ግድ የለኝም፤ እኔ እንኳ በራሴ ላይ አልፈርድም።

4 ኅሊናዬ ንጹሕ ነው፤ ይህ ግን ጥፋት አልባ መሆኔን አያረጋግጥም፤ በእኔ ላይ የሚፈርድ ጌታ ነው።

5 ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።

6 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ለእናንተ ጥቅም ብዬ በዚህ ጒዳይ እኔን ራሴንና አጵሎስን ምሳሌ አድርጌ አቅርቤላችኋለሁ፤ ይህንም ያደረግሁት፣ “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን ከእኛ እንድትማሩ ነው። ስለዚህ አንዱን ሰው ከሌላው አብልጣችሁ አትመኩበት።

7 ለመሆኑ፣ አንተን ከሌላው እንድትበልጥ ያደረገህ ማን ነው? ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ?

8 አሁንስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችኋል! ሀብታምም ሆናችኋል! ከእኛም ተለይታችሁ ነግሣችኋል! በርግጥ ብትነግሡማ እኛም ከእናንተ ጋር በነገሥን ነበር፤

9 ምክንያቱም እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን፣ ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሰው ሁሉ መጨረሻ ያሰለፈን ይመስለኛል፤ ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል።

10 እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን።

11 እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንደ በደባለን፤ ያለ መጠለያ እንንከራተታለን፤

12 በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን። ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤

13 ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን። እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጒድፍ፣ የምድር ጥራጊ ሆነናል።

14 ይህን የምጽፍላችሁ እንደ ተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ብዬ አይደለም።

15 ምንም እንኳ በዐሥር ሺህ የሚቈጠሩ ሞግዚቶች በክርስቶስ ቢኖሯችሁም፣ ብዙ አባቶች ግን የሏችሁም፤ በወንጌል አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ ወልጄአችኋለሁና።

16 ስለዚህ እኔን እንድትመስሉ እለምናችኋለሁ።

17 እንግዲህ በጌታ የተወደደውንና የታመነውን ልጄን ጢሞቴዎስን የላክሁላችሁ በዚህ ምክንያት ነው፤ እርሱም በየስፍራው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከማስተምረው ትምህርት ጋር የሚስማማውን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን የሕይወት አካሄዴን ያሳስባችኋል።

18 ከእናንተ አንዳንዶቹ ወደ እናንተ የማልመጣ መስሎአቸው ታብየዋል፤

19 ይሁን እንጂ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ ከዚያም እነዚህ ትዕቢተኞች የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን፣ ምን ኀይል እንዳላቸውም ማየት እሻለሁ።

20 ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት የወሬ ጒዳይ ሳይሆን የኀይል ጒዳይ ነው።

21 ለመሆኑ የምትፈልጉት የቱን ነው? በትር ይዤ ልምጣ? ወይስ በፍቅርና በገርነት መንፈስ?

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16