2 ቆሮንቶስ 7:7-13 NASV

7 የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል።

8 በመልእክቴ ባሳዝናችሁም በዚህ አልጸጸትም፤ ብጸጸትም እንኳ መልእክቴ ያሳዘናችሁ ለጥቂት ጊዜ እንደሆነ ተረድቻለሁ።

9 አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ ደስታዬም ስላዘናችሁ ሳይሆን፣ ሐዘናችሁ ንስሓ ለመግባት ስላበቃችሁ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተነሣ ምንም አልተጐዳችሁም።

10 እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል።

11 ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅናት፣ እንዴት ያለ ተግሣጽ እንዳ ስገኘላችሁ ተመልከቱ። በዚህም ጒዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል።

12 እንግዲህ እኔ የጻፍሁላችሁ ስለ በደለው ወይም ስለ ተበደለው ሰው አይደለም፤ ነገር ግን ለእኛ ምን ያህል ታማኞች እንደሆናችሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን እንድታዩ በማለት ነው።

13 እኛም የተጽናናነው በዚህ ምክንያት ነው።ከእኛም መጽናናት በተጨማሪ በቲቶ ደስታ እኛም ይበልጥ ደስ ብሎናል፤ ምክንያቱም ሁላችሁም መንፈሱን አሳርፋችኋል።