14 በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጒድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጒድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ።
15 ይህም፣ “ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂት የሰበሰበም አልጐደለበትም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
16 እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤
17 ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የመጣው ልመናችንን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ጒጒትና በራሱ ፈቃድ በመነሣሣት ነበር።
18 ከእርሱም ጋር በወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ልከነዋል።
19 ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ አብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጦአል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው።
20 በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን።