4 እነርሱም ቅዱሳንን ለመርዳት በሚደረገው አገልግሎት ለመሳተፍ ዕድል ያገኙ ዘንድ አጥብቀው ይለምኑን ነበር።
5 እኛ ከጠበቅ ነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ።
6 ስለዚህ ቲቶ፣ በእናንተ መካከል ቀደም ሲል የጀመረውን የልግስና ሥራ ከፍጻሜ እንዲያደርስ ለምነነው ነበር።
7 እናንተም በሁሉ ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በዕውቀት፣ በፍጹም ትጋትና ለእኛም ባላችሁ ፍቅር ልቃችሁ እንደ ተገኛችሁ፣ በዚህም የቸርነት ሥራ ልቃችሁ እንድትገኙ ዐደራ እንላችኋለን።
8 ይህን የምለው ትእዛዝ ለመስጠት ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን ሌሎች ከሚያሳዩት ትጋት አንጻር የፍቅራችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው።
9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።
10 ስለዚህ ጒዳይ የምሰጣችሁ ጠቃሚ ምክር ይህ ነው፤ ባለፈው ዓመት በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤