1 ሳሙኤል 1:15-21 NASV

15 ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ሰክሬ አይደለም፤ እኔ ልቧ ክፉኛ የታወከባት ሴት ነኝ፤ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት አፈሰስሁ እንጂ፣ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም።

16 ይህን ያህል ጊዜ የጸለይሁት ከባድ ከሆነው ጭን ቀቴና ሐዘኔ የተነሣ ስለ ሆነ፣ አገልጋይህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቊጠረኝ።”

17 ዔሊም፣ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” ሲል መለሰላት።

18 እርሷም፣ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።

19 በማግስቱ ጠዋት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤

20 ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤል አለችው።

21 ሰውየውም ሕልቃና ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት ስእለቱን ለማድረስ ቤተ ሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ሴሎ ወጣ።