4 ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር።
5 ሐናን ግን ይወዳት ስለ ነበር፣ ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር።
6 እግዚአብሔር ማሕፀኗን ስለ ዘጋም ጣውንቷ ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር።
7 ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ ሐና ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ታበሳጫት ነበር።
8 ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር።
9 አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።
10 ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች።