1 ሳሙኤል 12:9-15 NASV

9 “እነርሱ ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ረሱት፤ ስለዚህ ለሐጾር የጦር አዛዥ ለሲሣራ፣ ለፍልስጥኤማውያንና ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ሸጣቸው።

10 እነርሱም፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ እግዚአብሔርን ትተን በአሊምንና አስታሮትን አምልከናል። አሁን ግን ከጠላቶቻችን እጅ ታደገን፤ እኛም አንተን እናመልካለን’ ሲሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

11 ከዚያም እግዚአብሔር ይሩበኣልን፣ ባርቅን፣ ዮፍታሔንና ሳሙኤልን ልኮ በሰላም ትኖሩ ዘንድ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ እጅ ታደጋችሁ።

12 የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ ግን፣ ምንም እንኳ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ቢሆንም፣ ‘አይሆንም፤ የሚገዛን ንጉሥ እንፈልጋለን’ አላችሁ።

13 “አሁንም የጠየቃችሁትና የመረጣችሁት ንጉሥ ይኸው፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር በላያችሁ ንጉሥ አንግሦአል።

14 እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዛቱ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።

15 እግዚአብሔርን የማትታዘዙና በትእዛዛቱም ላይ የምታምፁ ከሆነ ግን፣ እጁ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ነበረች ሁሉ በእናንተም ላይ ትሆናለች።