1 ሳሙኤል 13:15-21 NASV

15 ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።

16 ፍልስጥኤማውያን በማክማስ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ ሳኦል፣ ልጁ ዮናታንና አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ነበሩ።

17 በሦስት ምድብ የተከፈሉ ወራሪዎች ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጡ፤ አንዱ ምድብ በሦጋል ግዛት ወደሚገኘው ወደ ዖፍራ አቀና፤

18 ሌላው ወደ ቤትሖሮን፣ ሦስተኛው ደግሞ በምድረ በዳው ትይዩ ካለው ከስቦይም ሸለቆ ቍልቍል ወደሚያሳየው ድንበር ዞረ።

19 ፍልስጥኤማውያን፣ “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር ለራሳቸው አይሥሩ” ብለው ስለ ነበር፣ በመላው የእስራኤል ምድር ብረት ቀጥቃጭ አልተገኘም።

20 ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ ማረሻቸውንና ዶማቸውን ለማሾል፣ ጠገራቸውንና ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርዱ ነበር።

21 ማረሻና ዶማ ለማሾል የሚከፈለው ዋጋ ሁለት ሦስተኛ ሰቅል ሲሆን፣ መንሽና ጠገራ እንዲሁም የበሬ መንጃ ለማሾል ደግሞ አንድ ሦስተኛ ሰቅል ነበር።