1 ሳሙኤል 14:27-33 NASV

27 ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ።

28 ከዚያም አንዱ ወታደር፣ “አባትህ ሰራዊቱን፣ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት በጽኑ መሓላ አስሮአል። ሰው ሁሉ የተዳከመው በዚሁ ምክንያት ነው” አለው።

29 ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሮአል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ።

30 ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቊጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።”

31 በዚያች ዕለት እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ እጅግ ዝለው ነበር።

32 በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፣ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት።

33 ከዚያም ለሳኦል፣ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው።ሳኦልም፣ “ሕግ ተላልፋችኋል፤ በሉ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አቅርቡልኝ” አለ።