1 ሳሙኤል 16:12-18 NASV

12 ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው።

13 ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ።

14 የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር።

15 የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው።

16 እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፣ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።”

17 ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

18 ከአገልጋዮቹም አንዱ፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፣ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ።