1 ሳሙኤል 17:17-23 NASV

17 በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ።

18 ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ።

19 እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።”

20 ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጒዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ።

21 እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር።

22 ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ።

23 ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ።