1 ሳሙኤል 17:37-43 NASV

37 ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።”ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን” አለው።

38 ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ጥሩር አጠለቀለት፤ ከናስ የተሠራ ቍርም ደፋለት።

39 ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፣ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤እርሱም ሳኦልን፣ “ያልተለማመድሁት ስለ ሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ሁሉንም አወለቀው።

40 ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፣ ወንጭፉን በእጁ ይዞ፣ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ።

41 ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ።

42 እርሱም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው።

43 ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው።