53 እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ።
54 ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማዊውን የጦር መሣሪያዎች በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ።
55 ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የሰራዊቱን አዛዥ አበኔርን፣ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው።አበኔርም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት።
56 ንጉሡም፣ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው።
57 ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ እንደ ተመለሰ፣ አበኔር ይዞ ንጉሡ ዘንድ አቀረበው። በዚህ ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ ነበር።
58 ሳኦልም፣ “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ሲል ጠየቀው።ዳዊትም፣ “እኔ የአገልጋይህ የቤተ ልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰ።