1 ሳሙኤል 18:17-23 NASV

17 ሳኦል ዳዊትን፣ “ታላቋ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የእግዚአብሔርንም ጦርነቶች ተዋጋ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፣ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበርና።

18 ዳዊት ግን ሳኦልን፣ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤም ሆነ የአባቴ ጐሣስ በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለው።

19 ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች።

20 በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው።

21 ሳኦልም በልቡ፣ “ወጥመድ እንድትሆነው፣ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን፣ “እነሆ፤ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው።

22 ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፣ “ለዳዊት፣ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለ ሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው።

23 እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ አማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቈጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እምብዛም የማልታወቅ ሰው ነኝ” አላቸው።