16 ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ ያለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር።
17 ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ።
18 ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር።
19 እናቱም ከባሏ ጋር ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር።
20 ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።
21 እግዚአብሔርም ሐናን ባረካት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።
22 በዚህ ጊዜ ዔሊ እጅግ አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በመላው እስራኤል ያደርጉ የነበረውን፣ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሰማ።