1 ሳሙኤል 2:18-24 NASV

18 ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር።

19 እናቱም ከባሏ ጋር ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር።

20 ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።

21 እግዚአብሔርም ሐናን ባረካት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

22 በዚህ ጊዜ ዔሊ እጅግ አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በመላው እስራኤል ያደርጉ የነበረውን፣ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሰማ።

23 ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ከመላው ሕዝብ እሰማለሁ፤ ለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?

24 ልጆቼ ሆይ፤ ትክክል አይደላችሁም፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ተሠራጭቶ የምሰማባችሁ ወሬ ጥሩ አይደለም።