1 ሳሙኤል 2:20-26 NASV

20 ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።

21 እግዚአብሔርም ሐናን ባረካት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

22 በዚህ ጊዜ ዔሊ እጅግ አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በመላው እስራኤል ያደርጉ የነበረውን፣ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሰማ።

23 ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ከመላው ሕዝብ እሰማለሁ፤ ለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?

24 ልጆቼ ሆይ፤ ትክክል አይደላችሁም፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ተሠራጭቶ የምሰማባችሁ ወሬ ጥሩ አይደለም።

25 አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል፣ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ይፈርዳል፤ ነገር ግን ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል፣ ማን ይማልድለታል?” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም።

26 ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ።