1 ሳሙኤል 22:1-7 NASV

1 ዳዊት ከጌት ወደ ዓዶላም ዋሻ ሸሸ፤ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰቦች ይህን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱ ወዳለበት ወደዚያው ወረዱ።

2 የተጨነቁ፣ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ አራት መቶ ያህል ሰዎች፣ ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፤ መሪያቸውም ሆነ።

3 ዳዊት ከዚያ ተነሥቶ፣ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ለሞዓብ ንጉሥ፣ እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ፣ አባቴና እናቴ መጥተው ካንተ ዘንድ እንዲቀመጡ ፈቃድህ ነውን?” አለው።

4 እርሱም በሞዓብ ንጉሥ ዘንድ አስቀመጣቸው፤ ዳዊት በዐምባ ውስጥ እስከ ቈየበትም ጊዜ ድረስ ከንጉሡ ዘንድ ተቀመጡ።

5 ይሁን እንጂ ነቢዩ ጋድ ዳዊትን፣ “በዐምባው ውስጥ አትቈይ፤ ሂድና ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ተነሥቶ ወደ ሔሬት ጫካ ገባ።

6 ሳኦልም፣ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን በሰማ ጊዜ፣ በጊብዓ ኰረብታ ላይ በአጣጥ ዛፍ ሥር፣ ጦሩን በእጁ ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ ሹማምቱም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር።

7 ሳኦልም እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የብንያም ሰዎች ስሙ! በውኑ የእሴይ ልጅ ዕርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን?