23 የሚደበቅባቸውን ቦታዎች ሁሉ ካያችሁ በኋላ ግልጽ መረጃ ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አብሬችሁ እሄዳለሁ፤ ብቻ በዚያ አገር ይገኝ እንጂ በይሁዳ ነገዶች ሁሉ መካከል ከገባበት ጒድጓድ ገብቼ አወጣዋለሁ።”
24 ስለዚህ ሰዎቹ ለመሄድ ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደ ዚፍ ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሴሞን በስተ ደቡብ በዓረባ ውስጥ ባለው በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ።
25 ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትን ሊፈልጉት ሄዱ፤ እርሱም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ ዐለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ። ሳኦልም ይህን እንደ ሰማ፣ ዳዊትን በማሳደድ ወደ ማዖን ምድረ በዳ ዘልቆ ገባ።
26 ሳኦል በተራራው በአንዱ በኩል ሆኖ ሲያሳድድ፣ ዳዊትና ሰዎቹ ደግሞ በተራራው በሌላ በኩል ከሳኦል ለማምለጥ ይጣደፉ ነበር። ሳኦልና ወታደሮቹ ዳዊትንና ሰዎቹን ከበው ለመያዝ ተቃርበው ሳሉ፣
27 አንድ መልእክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወረውታልና ቶሎ ድረስ!” አለው።
28 ከዚያም ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን ትቶ፣ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ሄደ። ከዚህ የተነሣም የዚያን ቦታ ስም “የመለያያ ዐለት” ብለው ጠሩት።
29 ዳዊትም ከዚያ ወደ ላይ ወጥቶ በዐይንጋዲ ምሽጎች ተቀመጠ።