8 ሳኦልም፣ ወደ ቅዒላ ወርደው ዳዊትንና ሰዎቹን እንዲከቡ፣ ሰራዊቱን በሙሉ ለጦርነት ጠራ።
9 ዳዊትም ሳኦል ክፉ እንዳሰበበት ባወቀ ጊዜ፣ ካህኑን አብያታርን፣ “ኤፉዱን አምጣ” አለው።
10 ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሳኦል ወደ ቅዒላ መጥቶ፣ በእኔ ምክንያት ከተማዪቱን ለማጥፋት ማሰቡን ባሪያህ በትክክል ሰምቶአል።
11 የቅዒላ ሰዎች አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? ባሪያህ እንደሰማውም ሳኦል ወደዚህ ይወርድ ይሆን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ እንድትነግረው እለምንሃለሁ።” እግዚአብሔርም፣ “አዎን ይወርዳል” አለው።
12 ዳዊትም እንደ ገና፣ “የቅዒላ ነዋሪዎች እኔንና ሰዎቼን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡናል?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን አሳልፈው ይሰጡአችኋል” አለው።
13 ስለዚህ ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎቹ ከቅዒላ ተነሥተው መሄድ ወደሚችሉበት ቦታ ሁሉ ሄዱ፤ ዳዊት ከቅዒላ መሸሹን በሰማ ጊዜ፣ ሳኦል ወደዚያ መሄዱን ተወ።
14 ዳዊት በምድረ በዳ ባሉ ምሽጎችና በዚፍ ምድረ በዳ ኰረብታዎች ተቀመጠ፤ ሳኦልም በየዕለቱ ይከታተለው ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳዊትን አሳልፎ አልሰጠውም።