17 አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተ ሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለ ሆነ፣ አስቢበትና የምታደርጊውን አድርጊ፤ እርሱ እንደሆነ እንዲህ ያለ ባለጌ ሰው ስለ ሆነ፣ ደፍሮ የሚነግረው አንድም ሰው የለም።
18 አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፣ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፣ አምስት የተሰናዱ በጎች፣ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰጠ እሸት፣ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፣ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች።
19 ከዚያም አገልጋዮቿን፣ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም።
20 እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው።
21 ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሮአል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ።
22 ነገ ጠዋት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፣ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!”
23 አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፣ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ተደፍታ እጅ ነሣች።