1 ሳሙኤል 25:8-14 NASV

8 የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ አመጣጣችን በጥሩ ቀን በመሆኑ፣ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ”

9 የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፣ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር።

10 ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው።

11 ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደ መጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?”

12 የዳዊት ሰዎችም ወደ መጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት።

13 ዳዊትም ሰዎቹን፣ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ።

14 ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረ በዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞች ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው።