1 ሳሙኤል 26:16-22 NASV

16 ያደረግኸው መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”

17 ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤

18 በመቀጠልም፣ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለምንድን ነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ?

19 አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባሪያውን ቃል ያድምጥ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፣ ቊርባን ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።

20 አንድ ሰው በተራራ ላይ ቆቅ እንደሚያድን የእስራኤልም ንጉሥ ቍንጫ ለመፈለግ ስለ ወጣ፣ ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።”

21 ሳኦልም፣ “በድያለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለ ከበረች፣ ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ በእርግጥ የሞኝ ሥራ ሠርቻለሁ፤ እጅግ ሲበዛም ተሳስቻለሁ” አለ።

22 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ጦር እነሆ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት።