1 ሳሙኤል 31:3-9 NASV

3 ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው እጅግ አቈሰሉት።

4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝ፣ እንዳያዋርዱኝ፣ አንተው ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው።ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፣ እምቢ አለው። ስለዚህ ሳኦል የራሱን ሰይፍ ወስዶ በላዩ ላይ ወደቀበት።

5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ባየ ጊዜ፣ እርሱም እንደዚሁ በሰይፉ ላይ ወድቆ አብሮት ሞተ።

6 ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ፣ አብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በዚያኑ ቀን ነበር።

7 በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰራዊት መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።

8 በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ሰዎች ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው።

9 ከዚያም የሳኦልን ራስ ቈርጠው፣ የጦር መሣሪያውንም ገፈው፣ የምሥራቹን በየቤተ ጣዖቶቻቸውና በሕዝባቸው መካከል እንዲናገሩ ወደ ፍልስጥኤም ምድር ሁሉ መልክተኞች ላኩ።